ዳንኤል 1:4-10 NASV

4 እነርሱም የአካል ጒዳት የሌለባቸው መልከ መልካሞች፣ ማንኛውንም ትምህርት የመማር ችሎታ ያላቸው፣ ዕውቀት የሞላባቸው፣ ሁሉን ነገር በፍጥነት መረዳት የሚችሉትንና በንጉሡም ቤት ለማገልገል ብቃት ያላቸው ወጣት ወንዶች ናቸው፤ የባቢሎናውያንን ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እንዲያስተምራቸውም አዘዘው።

5 ንጉሡም በየዕለቱ የሚበሉትን ምግብና የሚጠጡትን የወይን ጠጅ ከንጉሡ ማዕድ ድርጎ እንዲሰጣቸው አደረገ፤ ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ በንጉሡ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ናቸው።

6 ከነዚህም መካከል ከይሁዳ የመጡት ዳንኤል፣ አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ፤

7 የጃንደረቦቹ አለቃም አዲስ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣ አናንያን ሲድራቅ፤ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያን አብድናጎ ብሎ ጠራቸው።

8 ዳንኤል ግን በንጉሡ ምግብና የወይን ጠጅ እንዳይረክስ ወሰነ፤ በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ፈቃድ ጠየቀው።

9 እግዚአብሔርም ለዳንኤል በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ሞገስንና መወደድን ሰጠው።

10 ሆኖም የጃንደረቦቹ አለቃ ለዳንኤል፣ “መብሉንና መጠጡን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ብትታዩ፣ በንጉሡ ዘንድ በራሴ ላይ አደጋ ታስከትሉብኛላችሁ።” ብሎ ነገረው።