ዳንኤል 3:1-6 NASV

1 ንጉሡ ናቡከደነፆር ከፍታው ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።

2 ከዚያም መኳንንትን፣ ሹማምትን፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምንት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል እንዲመጡ ጠራ።

3 መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችና በየአውራጃው ያሉ ሹማምት ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል ተሰበሰቡ፤ በምስሉም ፊት ቆሙ።

4 ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፦

5 የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤

6 ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”