ዳንኤል 6:10-16 NASV

10 ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ።

11 ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው፣ ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማጸን አገኙት።

12 ወደ ንጉሡም ሄደው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ፣ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት።ንጉሡም፣ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ።

13 እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።

14 ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ።

15 ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት።

16 ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጒድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ” አለው።