ዳንኤል 6:13-19 NASV

13 እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።

14 ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ።

15 ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት።

16 ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጒድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ” አለው።

17 ድንጋይ አምጥተው በጒድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም፣ በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማኅተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች አተመበት።

18 ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ።

19 በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ እየተጣደፈ ሄደ።