1 የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በዐልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልም አለመ፤ ራእይም አየ፤ የሕልሙንም ዋና ሐሳብ ጻፈው።
2 ዳንኤል እንዲህ አለ፤ “አራቱ የሰማይ ነፋሳት ታላቁን ባሕር ሲያናውጡት ሌሊት በራእይ አየሁ፤
3 እርስ በርሳቸው የማይመሳሰሉ አራት ታላላቅ አራዊት ከባሕሩ ወጡ።
4 “የመጀመሪያው፣ አንበሳ ይመስል ነበር፤ የንስርም ክንፎች ነበሩት፤ ክንፎቹ እስኪነ ቃቀሉ ድረስ ተመለከትሁ፤ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ከምድር ከፍ ከፍ ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።
5 “እነሆም፤ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር፤ በአንድ ጐኑ ከፍ ብሎአል፤ በአፉ ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጐድን ዐጥንቶች ነበሩት። እርሱም፤ ‘ተነሥ፤ እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!’ ተባለ።