4 ኅሊናዬ ንጹሕ ነው፤ ይህ ግን ጥፋት አልባ መሆኔን አያረጋግጥም፤ በእኔ ላይ የሚፈርድ ጌታ ነው።
5 ስለዚህ ጊዜው ሳይደርስ በምንም ነገር አትፍረዱ፤ ጌታ እስኪመጣ ጠብቁ። እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል። በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ምስጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል።
6 እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ለእናንተ ጥቅም ብዬ በዚህ ጒዳይ እኔን ራሴንና አጵሎስን ምሳሌ አድርጌ አቅርቤላችኋለሁ፤ ይህንም ያደረግሁት፣ “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ከእኛ እንድትማሩ ነው። ስለዚህ አንዱን ሰው ከሌላው አብልጣችሁ አትመኩበት።
7 ለመሆኑ፣ አንተን ከሌላው እንድትበልጥ ያደረገህ ማን ነው? ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?
8 አሁንስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል! ሀብታምም ሆናችኋል! ከእኛም ተለይታችሁ ነግሣችኋል! በርግጥ ብትነግሡማ እኛም ከእናንተ ጋር በነገሥን ነበር፤
9 ምክንያቱም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን፣ ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሰው ሁሉ መጨረሻ ያሰለፈን ይመስለኛል፤ ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል።
10 እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።