1 ቆሮንቶስ 4:9-15 NASV

9 ምክንያቱም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን፣ ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሰው ሁሉ መጨረሻ ያሰለፈን ይመስለኛል፤ ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል።

10 እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።

11 እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደ በደባለን፤ ያለ መጠለያ እንንከራተታለን፤

12 በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን። ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤

13 ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን። እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጒድፍ፣ የምድር ጥራጊ ሆነናል።

14 ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም።

15 ምንም እንኳ በዐሥር ሺህ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና።