1 ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
2 እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።
3 ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን።
4 “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።
5 ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤
6 ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።
7 ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው።