1 ጢሞቴዎስ 5:10-16 NASV

10 ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት።

11 ወጣት መበለቶችን ግን እንዲህ ባለው መዝገብ አትጻፋቸው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ በገቡት ቃል ላይ በሚያይልበት ጊዜ ለማግባት ይሻሉና።

12 በዚህም ፍርድን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በመጀመሪያ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።

13 በተጨማሪም ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጒዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።

14 ስለዚህ ባል የሞተባቸው ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ጠላትም የሚነቅፍባቸውን ነገር እንዳያገኝ እመክራለሁ።

15 በርግጥ ከዚህ በፊት አንዳንዶቹ ሰይጣንን ለመከተል ዘወር ብለዋል።

16 አማኝ የሆነች ማንኛዋም ሴት በቤተ ሰቧ ውስጥ መበለቶች ቢኖሯት፣ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ መበለቶችን ብቻ መርዳት እንድትችል እርሷው ትርዳቸው እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ሸክም እንዲሆኑ አትተዋቸው።