1 በእግዚአብሔር ፊት እንዲሁም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት፣ መገለጡንና መንግሥቱን በማሰብ ይህን ዐደራ እልሃለሁ፤
2 ቃሉን ስበክ፤ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግሥትና በማስተማር አቅና፤ ገሥጽ፤ አበረታታም።
3 ምክንያቱም ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።
4 እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።
5 አንተ ግን በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ መከራን ታገሥ፤ የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም።
6 እኔ እንደ መጠጥ ቊርባን መሥዋዕት ለመፍሰስ ተቃርቤአለሁ፤ ተለይቼ የምሄድበት ጊዜ ደርሶአል።
7 መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ።