ሐዋርያት ሥራ 11:12-18 NASV

12 መንፈስ ቅዱስም ምንም ሳላወላውል ከእነርሱ ጋር እንድሄድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስት ወንድሞች ከእኔ ጋር ሄዱ፤ ወደ ሰውየውም ቤት ገባን።

13 እርሱም መልአክ በቤቱ ውስጥ ቆሞ እንደ ታየውና እንዲህ እንዳለው ነገረን፤ ‘ወደ ኢዮጴ ሰው ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስጠራ፤

14 እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ቃል ይነግርሃል።’

15 “እኔም ገና መናገር ስጀምር፣ መንፈስ ቅዱስ፣ በመጀመሪያ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ በእነርሱም ላይ ወረደ።

16 በዚህ ጊዜ፣ ‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ሲል ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለኝ።

17 እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን ለእኛ የሰጠንን ስጦታ ለእነርሱም ከሰጣቸው፣ ታዲያ፣ እግዚአብሔርን መቋቋም እችል ዘንድ እኔ ማን ነኝ?”

18 ይህን በሰሙ ጊዜም የሚሉትን አጥተው እንዲህ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ “ይህማ ከሆነ፣ አሕዛብም ወደ ሕይወት ይመጡ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን ሰጥቷቸዋል ማለት ነዋ።”