4 በርናባስና ሳውልም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።
5 ስልማና በደረሱም ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ዮሐንስም አብሮአቸው ሆኖ ይረዳቸው ነበር።
6 የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር አቋርጠው ጳፉ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤
7 እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው።
8 ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጒም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዡ እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው።
9 ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤
10 “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?