7 እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው።
8 ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጒም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዡ እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው።
9 ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤
10 “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?
11 አሁንም የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውር ትሆናለህ፤ ከእንግዲህ የፀሓይን ብርሃን ለአንድ አፍታ እንኳ አታይም።”ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ በላዩ ወረደ፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ለመፈለግ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር።
12 አገረ ገዡም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ በጌታ ትምህርት በመደነቅ አመነ።
13 ጳውሎስና ጓደኞቹ ከጳፉ ተነሥተው በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌን ሄዱ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።