ሐዋርያት ሥራ 16:11-17 NASV

11 ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጒዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጒዞአችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤

12 ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን።

13 በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን።

14 ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ፣ ልቧን ከፈተላት።

15 እርሷና ቤተ ሰዎቿ ከተጠመቁ በኋላም፣ “በጌታ ማመኔን በርግጥ ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ጥቂት ተቀመጡ” በማለት አጥብቃ ለመነችን።

16 አንድ ቀን ወደ ጸሎት ስፍራ ስንሄድ፣ በጥንቈላ መንፈስ ትንቢት የምትናገር አንዲት የቤት አገልጋይ አገኘችን፤ እርሷም በዚህ የጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው ነበር።

17 ይህችው አገልጋይ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ፣ የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው!” በማለት ትጮኽ ነበር፤