ሐዋርያት ሥራ 17:15-21 NASV

15 ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት፤ ከዚያም ሲላስና ጢሞቴዎስ ወደ እርሱ በፍጥነት እንዲመጡ የሚል ትእዛዝ ተቀብለው ተመለሱ።

16 ጳውሎስ በአቴና ሆኖ ሲጠብቃቸው ሳለ፣ ከተማዪቱ በጣዖት የተሞላች መሆኗን በማየት መንፈሱ ተበሳጨበት።

17 ስለዚህ በምኵራብ ሆኖ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ግሪኮች ጋር፣ ደግሞም በገበያ ስፍራ ዕለት ዕለት ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር።

18 ከኤፊቆሮስና ከኢስጦኢክ የፍልስፍና ወገን የሆኑትም ወደ እርሱ መጥተው ይከራከሩት ነበር። አንዳንዶቹ፣ “ይህ ለፍላፊ ምን ለማለት ይፈልጋል?” ይሉ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው የምሥራች ሲሰብክ ሰምተው፣ “ስለ አዳዲስ ባዕዳን አማልክት የሚናገር ይመስላል” አሉ።

19 ይዘውም አርዮስፋጎስ ወደተባለው ስፍራ በመውሰድ እንዲህ አሉት፤ “አንተ የምታስተምረው ይህ አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ እንድናውቅ ትፈቅዳለህን?

20 ደግሞም በጆሮአችን የምታሰማን እንግዳ ነገር ስለ ሆነብን፣ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።”

21 የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጒዳይ አልነበረም።