ሐዋርያት ሥራ 17:23-29 NASV

23 እየተዘዋወርሁ ሳለሁ፣ የምታመልኳቸውን ነገሮች ስመለከት፣ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ ያለበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁና፤ እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እገልጽላችኋለሁ።

24 “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም።

25 እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም።

26 የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው።

27 ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤

28 የምንኖረውና የምንንቀሳቀ ሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና። ከራሳችሁ ባለቅኔዎችም አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ‘እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን።’

29 “እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ አምላክ በሰው ሙያና ጥበብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ ይመስላል ብለን ማሰብ አይገባንም።