11 ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማራቸው አንድ ዓመት ተኩል አብሮአቸው ተቀመጠ።
12 ጋልዮስ የአካይያ ገዥ በነበረበት ጊዜ አይሁድ ተባብረው በጳውሎስ ላይ ተነሡ፤ ፍርድ ወንበር ፊት አቅርበውትም፣
13 “ይህ ሰው ሕጉ በማይፈቅደው መንገድ፣ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ እያሳሳታቸው ነው” አሉ።
14 ጳውሎስ ሊናገር ገና አፉን ሲከፍት፣ ጋልዮስ አይሁድን እንዲህ አላቸው፤ “የአይሁድ ሰዎች ሆይ፤ ያቀረባችሁት ጒዳይ ስለ ዐመፅ ወይም ስለ ከባድ ወንጀል ቢሆን ኖሮ ላዳምጣችሁ በተገባኝ ነበር፤
15 ነገር ግን ክርክራችሁ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች እንዲሁም ስለ ሕጋችሁ በመሆኑ፣ እናንተው ጨርሱት፤ እኔ በእንዲህ ዐይነት ነገር ፈራጅ ለመሆን አልሻም።”
16 ስለዚህ ከፍርድ ወንበር ፊት አስወጣቸው።
17 በዚህ ጊዜ ሁሉም የምኵራቡን አለቃ፣ ሶስቴንስን ይዘው በፍርድ ቤቱ ፊት ደበደቡት፤ ጋልዮስ ግን ነገሩ ደንታም አልሰጠውም።