ሐዋርያት ሥራ 18:2-8 NASV

2 በዚያም የጳንጦስ ተወላጅ የሆነውን፣ አቂላ የተባለውን አይሁዳዊ አገኘ፤ እርሱም አይሁድ ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ቀላውዴዎስ ባዘዘው መሠረት ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር በቅርብ ጊዜ ከኢጣሊያ የመጣ ነበር። ጳውሎስም ሊያያቸው ወደ እነርሱ ሄደ፤

3 እርሱም እንደ እነርሱ ድንኳን ሰፊ ስለ ነበረ፣ ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ተሰማራ።

4 በየሰንበቱም ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ጋር በምኵራብ ውስጥ እየተነጋገረ ሊያሳምናቸው ይጥር ነበር።

5 ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ በወረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስ በስብከት እየተጋ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ለአይሁድ ይመሰክር ነበር።

6 ነገር ግን በተቃወሙትና በሰደቡት ጊዜ ልብሱን አራግፎ፣ “ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን! እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ” አላቸው።

7 ከዚያም ወጥቶ ቲቶስ ኢዮስጦስ ወደተባለ፣ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ፤ የዚህም ሰው ቤት በምኵራቡ አጠገብ ነበር።

8 የምኵራብ አለቃ የነበረው ቀርስጶስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ፤ ጳውሎስ ሲናገር የሰሙ ብዙ የቆሮንቶስ ሰዎችም አምነው ተጠመቁ።