11 ተመልሶም እንደ ገና ወደ ፎቁ ወጣ፤ እንጀራውንም ቈርሶ በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ብዙ ከተናገረ በኋላ ተነሥቶ ሄደ።
12 ሰዎችም ያን ጐበዝ ሕያው ሆኖ ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ።
13 እኛ ግን ጳውሎስን ለመቀበል ቀድመን ወደ መርከቡ ሄድን፤ ከዚያም በመርከብ ወደ አሶን ተጓዝን፤ ይህን ያደረግነውም ጳውሎስ በየብስ በእግሩ ሊሄድ ስላሰበ ነበር።
14 በአሶን ከተገናኘንም በኋላ፣ ተቀብለነው አብረን በመርከብ ወደ ሚጢሊኒ ሄድን።
15 በማግስቱም በመርከብ ተጒዘን ከኪዩ ደሴት ትይዩ ደረስን። በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን።
16 ጳውሎስም በእስያ አውራጃ ብዙ መቈየት ስላልፈለገ፣ ወደ ኤፌሶን ሳይ ገባ ዐልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ቢቻል በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ለመዋል ቸኵሎ ነበርና።
17 ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ሰው ልኮ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሽማግሌዎች አስጠራ፤