4 የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሱሲጳጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና ሲኮን ዱስ፣ የደርቤኑ ጋይዮስ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ፣ እንዲሁም ጢሞቴዎስ አብረውት ሄዱ።
5 እነዚህም ሰዎች ወደ ፊት ቀድመውን በጢሮአዳ ጠበቁን።
6 እኛ ግን፣ የቂጣ በዓል ካለፈ በኋላ፣ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሣን፤ ከአምስት ቀንም በኋላ ከሌሎቹ ጋር በጢሮአዳ ተገናኘን፤ በዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን።
7 በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቊረስ ተሰብስበን ሳለን፣ ጳውሎስ በማግስቱ ለመሄድ ስላሰበ፣ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ።
8 በተሰበሰብንበትም ሰገነት ላይ ብዙ መብራት ነበር።
9 አውጤኪስ የተባለ አንድ ጐበዝም በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አለውና ጭልጥ ብሎ ተኛ፤ ከሦስተኛውም ፎቅ ቊልቊል ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት።
10 ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ተጋድሞ ዐቀፈውና፣ “ሕይወቱ በውስጡ ስላለች ሁከት አትፍጠሩ” አላቸው።