1 አግሪጳም ጳውሎስን፣ “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መከላከያውን አቀረበ፤
2 “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤
3 ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ።
4 “ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤
5 ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ።