1 ወደ ኢጣሊያ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎቹን እስረኞች የንጉሠ ነገሥቱ ክፍለ ጦር አባል ለሆነው፣ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቧቸው።
2 ከአድራሚጢስ ተነሥቶ በእስያ አውራጃ ባሕር ዳርቻ ላይ ወዳሉት ወደቦች በሚሄደው መርከብ ተሳፍረን የባሕር ጒዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ ይኖር የነበረው የመቄዶንያ ሰው፣ አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ነበረ።
3 በሚቀጥለው ቀን ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት በማሳየት ወደ ወዳጆቹ ሄዶ ርዳታ እንዲቀበል ፈቀደለት።
4 ከዚያም ተነሥተን በባሕር ተጓዝን፤ ነፋስ ከፊት ለፊት ስለገጠመን፣ የቆጵሮስን ደሴት ተገን አድርገን ዐለፍን።
5 በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ አገር ሙራ የተባለ ቦታ ደረስን።