20 እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር የጠራኋችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”
21 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም።
22 ይሁን እንጂ፣ ሰዎች ስለዚህ የእምነት ክፍል በየቦታው ክፉ እንደሚያወሩበት እናውቃለን፤ የአንተ አስተያየት ደግሞ ምን እንደሆነ መስማት እንፈልጋለን።”
23 ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ፣ ብዙ ሆነው ወደ ማረፊያ ስፍራው መጡ፤ እርሱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ሞከረ።
24 አንዳንዶቹ እርሱ የሚለውን አምነው ተቀበሉ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑበትም፤
25 እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም፤ ጳውሎስም እንዲህ የሚል የመጨረሻ ቃል ከተናገራቸው በኋላ ሄዱ፤ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፤
26 “ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ እንዲህም በላቸው፤“መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ማየትን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትመለከቱም።”