2 ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤
3 እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው።
4 ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስቲ ወደ እኛ ተመልከት” አለው።
5 ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት አስቦ በትኵረት ተመለከታቸው።
6 ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤
7 ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ፤
8 ዘሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ።