1 ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ፣ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ኀላፊ እንዲሁም ሰዱቃውያን ድንገት ወደ እነርሱ መጡ።
2 እነርሱም ሐዋርያት ሕዝቡን በማስተማራቸውና በኢየሱስ ስለተገኘው ትንሣኤ ሙታን በመስበካቸው እጅግ ተቈጡ።
3 ጴጥሮስና ዮሐንስን ያዟቸው፤ ጊዜውም ምሽት ስለ ነበረ እስኪነጋ ድረስ ወህኒ ቤት አሳደሯቸው።
4 ይሁን እንጂ ቃሉን ከሰሙት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ።
5 በማግስቱም አለቆቻቸውና፣ ሽማግሌዎቻቸው እንዲሁም ጸሓፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።
6 ሊቀ ካህናቱ ሐና፣ ቀያፋ፣ ዮሐንስ፣ እስክንድሮስና የሊቀ ካህናቱ ቤተ ዘመዶች ሁሉ በዚያ ተገኝተው ነበር።