15 ስለዚህ ከሸንጎው እንዲያወጧቸው አዘዙ፤ ከዚያም በአንድነት ተሰብስበው ተመካከሩ፤
16 እንዲህም ተባባሉ፤ “እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? በኢየሩሳሌም የሚኖር ሁሉ በእነርሱ እጅ የተደረገውን ድንቅ ታምር ዐውቆአል፣ ስለዚህ ይህንን ማስተባበል አንችልም፤
17 ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር ከእንግዲህ በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ፣ እነዚህም ሰዎች ዳግመኛ በዚህ ስም ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።”
18 ከጠሯቸውም በኋላ፣ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው።
19 ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤
20 እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።”
21 እንደ ገና ከዛቱባቸው በኋላም ለቀቋቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ስለ ነበር ሊቀጧቸው አልቻሉም፤