26 የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ገዦችም በአንድነት ተሰበሰቡ፤በጌታ ላይ፣በተቀባውም ላይ ተከማቹ።’
27 በርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ፤
28 ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።
29 አሁንም ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው።
30 ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ።”
31 ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።
32 ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም።