34 ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤
35 ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል።
36 ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ።
37 ከእርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ።
38 ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ አትንኳቸው፤ ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤
39 ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”
40 እነርሱም ምክሩን ተቀብለው፤ ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዘው ለቀቋቸው።