5 በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታህል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከእርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት።
6 ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ቀንበር ሥር ይማቅቃል።
7 ሆኖም በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ። ከዚያም አገር ወጥተው በዚህች ስፍራ ያመልኩኛል።’
8 ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።
9 “የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣
10 ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብፅም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብፅና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።
11 “በዚያ ጊዜም በግብፅና በከነዓን አገር ሁሉ፣ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን አጡ።