24 ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችሁት ምንም ነገር እንዳይደርስብኝ ጌታን ለምኑልኝ” አላቸው።
25 ጴጥሮስና ዮሐንስም የጌታን ቃል ከመሰከሩና ገልጠው ከተናገሩ በኋላ፣ በብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን እየሰበኩ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
26 የጌታም መልአክ ፊልጶስን፣ “ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ” አለው፤
27 እርሱም ተነሥቶ ሄደ። እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟልና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ። ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር።
28 ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።
29 መንፈስም ፊልጶስን፣ “ሂድ፤ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።
30 ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሄደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ፣ “ለመሆኑ፣ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው።