15 ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ።አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።
16 ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል!” አለ።
17 ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር
18 ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና።
19 ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም።
20 ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር።
21 በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ።