3 ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፣ በሥርዐቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና።
4 ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፣ ማሰሮን፣ ሳሕንና ዐልጋን እንደ ማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር።
5 ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት።
6 እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣ ስለ ግብዞች በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
7 በከንቱ ያመልከኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው።’
8 የእግዚአብሔርን ትእዝዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዐት ታጠብቃላችሁ።”
9 ደግሞም፣ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ አላችሁ።