10 እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
11 ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት።
12 ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል?
13 ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።”
14 ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው፣ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ።
15 ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ።
16 እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጒዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው።