16 “ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤
17 “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም’
18 ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና።
19 የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች።”
20 ከዚያም ኢየሱስ ብዙውን ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ንስሓ ባለመግባታቸው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው፤
21 “ወዮልሽ ኮራዚን፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር።
22 ስለዚህ እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል።