5 ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤
6 በእኔ የማይሰናከልም ብፁዕ ነው።”
7 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸምበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ?
8 ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ።
9 ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይ ልታዩ? አዎን፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።
10 እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘በፊትህ መንገድህን ያዘጋጅልህ ዘንድ፣ ከአንተ አስቀድሜ መልእክተኛዬን እልካለሁ።’
11 እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።