ማቴዎስ 5:14-20 NASV

14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤

15 ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ።

16 እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።

17 “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።

18 እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም።

19 ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዛት አነስተኛዪቱን እንኳን ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዛት እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል።

20 ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።