23 “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣
24 መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።
25 “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ።
26 እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።
27 “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
28 እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዓይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል።
29 ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።