30 ቀኝ እጅህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።
31 “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
32 እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቈጠራል።
33 “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በእግዚአብሔር ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
34 እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤
35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና
36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና።