ማቴዎስ 9:16-22 NASV

16 “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል።

17 በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደህና ተጠብቀው ይቈያሉ።”

18 ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ ሹም ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው።

19 ኢየሱስም ተነሥቶ አብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

20 ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት ከኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ነካች።

21 እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር።

22 ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፤ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች።