ራእይ 11:12-18 NASV

12 ከዚያም፣ “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቷቸው በደመና ወደ ሰማይ ወጡ።

13 በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማዪቱም አንድ ዐሥረኛ ወደመ፤ በነውጡም ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ የተረፉትንም ፍርሀት ያዛቸው፤ ለሰማይም አምላክ ክብር ሰጡ።

14 ሁለተኛው ወዮ ዐልፎአል፤ እነሆ፤ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል።

15 ሰባተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በሰማይም እንዲህ የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ፤“የዓለም መንግሥት፣የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”

16 በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግምባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤

17 እንዲህም አሉ፤“ያለህና የነበርህ፣ሁሉን ቻይ፤ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እናመሰግንሃለን፤ምክንያቱም አንተ ታላቁን ኀይልህን ይዘህ ነግሠሃል።

18 አሕዛብ ተቈጥተው ነበር፤የአንተም ቍጣ መጣች፤በሙታን ላይ የምትፈርድበት፣ለአገልጋዮችህ ለነብያት፣ለቅዱሳንና ስምህን ለሚፈሩት፣ለታናናሾችና ለታላላቆች ዋጋቸውን የምትሰጥበት፣ምድርንም ያጠፏትን የምታጠፋበት ዘመን መጣ።”