1 ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ።
2 ከሰማይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁት ድምፅ በገና ደርዳሪዎች እንደሚደረድሩት ዐይነት ነበረ።
3 እነርሱም በዙፋኑ ፊት፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ መዝሙር ዘመሩ። ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች በስተቀር መዝሙሩን ማንም ሊማረው አልቻለም።
4 እነዚህ ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱት ናቸው፤ ራሳቸውን በንጽሕና ጠብቀዋልና። በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው።
5 በአፋቸው ምንም ዐይነት ውሸት አልተገኘም፤ ነቀፋም የለባቸውም።
6 ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤
7 በታላቅ ድምፅም፣ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” አለ።
8 ሌላም ሁለተኛ መልአክ፣ “ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች ወደቀች!” እያለ ተከተለው።
9 ሦስተኛውም መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ማንም ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ፣ ምልክቱንም በግምባሩ ወይም በእጁ ላይ የሚቀበል ቢኖር፣
10 እርሱ ደግሞ ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት በቍጣው ጽዋ ውስጥ የተሞላውን የእግዚአብሔርን ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል። በቅዱሳን መላእክትና በበጉ ፊትም በእሳትና በዲን ይሠቃያል።
11 የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ ወይም የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።”
12 የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው።
13 ከዚያም፣ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ ሆነው የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማሁ። መንፈስም፣ “አዎ፣ ሥራቸው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ያርፋሉ” ይላል።
14 አየሁም፤ እነሆ፤ በፊቴ ነጭ ደመና ነበረ፤ በደመናውም ላይ፣ “የሰውን ልጅ የሚመስል” ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቶ፣ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር።
15 ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፣ “የዐጨዳው ሰዓት ስለ ደረሰ፣ ማጭድህን ይዘህ ዕጨድ፤ የምድር መከር ደርሶአልና” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
16 ስለዚህ በደመናው ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች።
17 ሌላም መልአክ በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም እንዲሁ ስለታም ማጭድ ነበረው፤
18 በእሳት ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ የያዘውን፣ “ዘለላው ስለ በሰለ፣ ስለታም ማጭድህን ያዝና በምድር ላይ ያሉትን የወይን ዘለላዎች ሰብስብ” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
19 መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ የምድርን የወይን ዘለላዎች ሰብስቦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር የቍጣ ወይን መጭመቂያ ጣላቸው።
20 ወይኑም ከከተማው ውጭ በወይን መጭመቂያ ውስጥ ተረገጠ፤ ከፍታው እስከ ፈረስ ልጓም የሚደርስ፣ ርዝመቱ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ያህል ደም ከመጭመቂያው ወጣ።