1 ዘንዶውም በባሕሩ ዳር ቆሞ ነበር።ከዚያም አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች፣ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩት።
2 ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ ነገር ግን እግሮቹ የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር፤ ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው።
3 ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቊስል ያለበት ይመስል ነበር። ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቊስሉ ዳነ፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለው።
4 ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለአውሬው ሰጥቶታል። ደግሞም፣ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት ለአውሬው ሰገዱለት።
5 አውሬው የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት።
6 እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣ በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ።
7 ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድልም እንዲነሣቸው ኀይል ተሰጠው። በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።
8 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ።
9 ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።
10 ማንም የሚማረክ ቢኖር፣እርሱ ይማረካል፤ማንም በሰይፍ የሚገድል ቢኖር፣እርሱ በሰይፍ ይገደላል።ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደሆነ ያስገነዝባል።
11 ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገር ነበር።
12 በመጀመሪያው አውሬ ስም በሙሉ ሥልጣን ይሠራ ነበር፤ ምድርና በእርሷም የሚኖሩ ሁሉ፣ ለሞት ከሚያደርሰው ቊስል የዳነውን የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ አደረገ።
13 በሰዎቹም ፊት እሳት ከሰማይ ወደ ምድር እስኪያወርድ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችን አደረገ።
14 በመጀመሪያው አውሬ ስም ምልክቶችን እንዲያደርግ ሥልጣን ስለ ተሰጠው፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎችን አሳተ፤ በሰይፍ ቆስሎ ለነበረው፣ ነገር ግን በሕይወት ለሚኖረው አውሬ ምስል እንዲያቆሙም አዘዛቸው።
15 ደግሞም የመጀመሪያው አውሬ ምስል መናገር እንዲችል ለምስሉ እስትንፋስ ለመስጠትና ለዚህም ምስል የማይሰግዱ ሁሉ እንዲገደሉ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው።
16 እንዲሁም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድኾች፣ ጌቶችና ባሮች ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ላይ ምልክት እንዲቀበሉ አስገደዳቸው፤
17 ይህም የሆነው የአውሬው ምልክት፣ ይኸውም ስሙ ወይም የስሙ ቍጥር የሌለው ማንም ሰው ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ እንዳይችል ነው።
18 ይህ ጥበብ ይጠይቃል፤ አእምሮ ያለው ማንኛውም ሰው የአውሬውን ቍጥር ያስላው፤ ምክንያቱም ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነው። ቍጥሩ ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት ነው።