ራእይ 6 NASV

ማኅተሞቹ

1 በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲፈታ አየሁ፤ ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ፣ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ።

2 እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ።

3 በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ።

4 ሌላ ፍም የሚመስል ቀይ ፈረስም ወጣ፤ ተቀምጦበት የነበረው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድና ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅም ሰይፍ ተሰጠው።

5 በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ጥቍር ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር።

6 ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን መካከል፣ “አንድ እርቦ ስንዴ ለአንድ ቀን ደመወዝ፤ ሦስት እርቦ ገብስም ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጒዳ” የሚል ድምፅ ሰማሁ።

7 በጉ አራተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ አራተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ።

8 እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረው ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።

9 አምስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁትም ምስክርነት የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ።

10 እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ “ሁሉን የምትገዛ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?” አሉ።

11 ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።

12 ስድስተኛውን ማኅተም ሲፈታ ተመለከትሁ፤ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሓይም እንደ ማቅ ጠቈረች። ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፤

13 የበለስ ዛፍ በብርቱ ነፋስ ስትወዛወዝ ያልበሰለው ፍሬ ከእርሷ እንደሚረግፍ፣ የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ረገፉ።

14 ሰማይ እንደ ጥቅልል መጽሐፍ ተጠቅልሎ ዐለፈ፤ ተራሮችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወገዱ።

15 ከዚህ በኋላ የምድር ነገሥታትና ገዦች፣ የጦር መኰንኖች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሮችና ጌቶች ሁሉ በዋሻዎችና በተራሮች ዐለት ውስጥ ተሸሸጉ፤

16 ተራሮቹንና ዐለቶቹንም፣ “በላያችን ውደቁ፤ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቊጣ ሰውሩን፤

17 ታላቁ የቊጣቸው ቀን መጥቶአልና፤ ማንስ ሊቆም ይችላል?” አሏቸው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22