ራእይ 11:2-8 NASV

2 የውጭውን አደባባይ ግን ተወው፤ አትለካው፤ ለአሕዛብ የተሰጠ ነውና። እነርሱ የተቀደሰችውን ከተማ አርባ ሁለት ወር ይረግጧታል።

3 ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።”

4 እነዚህም በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙት ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።

5 ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ፣ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያጠፋል፤ ሊጐዳቸው የሚፈልግ ሁሉ መሞት ያለበት በዚህ ዐይነት ነው።

6 እነዚህ ሰዎች ትንቢት በሚናገሩባቸው ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ ደግሞም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ ምድርን በማንኛውም መቅሠፍት ለመምታት ሥልጣን አላቸው።

7 ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ድል ይነሣቸዋል፤ ይገድላቸዋልም።

8 ሬሳቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት።