ራእይ 18:2-8 NASV

2 እርሱም በብርቱ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፤“ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!የአጋንንት መኖሪያ፣የርኩሳን መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣የርኩስና የአስጸያፊ ወፎች ሁሉ መጠለያ ሆነች።

3 ሕዝቦች ሁሉ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤የምድር ነገሥታት ከእርሷ ጋር አመንዝረዋል፤የምድርም ነጋዴዎች ከብዙ ምቾቷ ኀይልየተነሣ በልጽገዋል።”

4 ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤“ሕዝቤ ሆይ፤ በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ከእርሷ ውጡ፤

5 ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሮአልና፤እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሶአል።

6 በሰጠችው መጠን ብድራቷን መልሱላት፤ለሠራችው ሁሉ ዕጥፍ ክፈሏት፤በቀላቀለችውም ጽዋ ዕጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።

7 ለራሷ ክብርና ምቾት የሰጠችውን ያህል፣ሥቃይና ሐዘን ስጧት፤በልቧም እንዲህ እያለች ትመካለች፤“እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤መበለትም አይደለሁም፤ ከቶምአላዝንም፤”

8 ስለዚህ መቅሠፍቶቿ በአንድ ቀን ይመጡባታል፤ሞት፣ ሐዘንና ራብ ይሆኑባታል፤የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ስለ ሆነ፣በእሳት ትቃጠላለች።