ራእይ 21:5-11 NASV

5 በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለ።

6 እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ።

7 ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።

8 ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኵሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”

9 ሰባቱ የመጨረሻ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” አለኝ።

10 በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅና ረጅም ተራራ ወስዶኝ፣ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።

11 እርሷም በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር።