ራእይ 5:4-10 NASV

4 እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ።

5 ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቶአል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።

6 ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።

7 እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ።

8 መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።

9 እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤“መጽሐፉን ልትወስድ፣ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ምክንያቱም ታርደሃል፤በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።

10 ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”