15 እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ።የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት።
16 በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤
17 እርሱም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በአራማይክ ‘ጎልጎታ’ ተብሎ ወደሚጠራው ‘የራስ ቅል’ ወደተባለው ቦታ ወጣ።
18 በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር ሁለት ሰዎች፣ አንዱን በዚህ በኩል፣ ሌላውን በዚያ በኩል፣ ኢየሱስንም በመካከል አድርገው ሰቀሉ።
19 ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ’ የሚል ነበር።
20 ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር።
21 የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት።