ዮሐንስ 20:19-25 NASV

19 በዚያኑ ዕለት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት፣ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮቹን ቈልፈው ተሰብስበው ሳለ፣ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

20 ይህንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርትም ጌታን ባዩት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው።

21 ኢየሱስም እንደ ገና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እኔን እንደ ላከኝ፣ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው።

22 ይህን ካለ በኋላም፣ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፤ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤

23 የሰዎችን ኀጢአት ይቅር ብትሉ፣ ኀጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል፤ ኀጢአታቸውን ይቅር ባትሉ ግን፣ ይቅር አይባልላቸውም።”

24 በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አልነበረም።

25 ሌሎች ደቀ መዛሙርትም፣ “ጌታን አየነው እኮ!” አሉት።እርሱ ግን፣ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ።