8 ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ።
9 ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ።
10 ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው።
11 ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም።
12 ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም።
13 ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ዓሣውንም ሰጣቸው።
14 እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።